አርች ኮልድ ሶልሽንስ ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለመተግበር ፍላጎት ማሳየቱ ተጠቆመ | Ethiopian Reporter Tenders | 2merkato | ጨረታ

መሠረቱን በእንግሊዝ አገር ያደረገና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ድጋፍ የሚንቀሳቀስ አርች ኮልድ ሶልሽንስ የተባለ ድርጀት ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የማቀዝቀዣ መጋዘን ግንባታ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለመተግበር ፍላጎት ማሳየቱ ተጠቆመ፡፡

ድርጅቱ በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ የማቀዝቀዣ መጋዘን (የኮልድ ቼይን ፋሲሊቲ) የሚያቀርብ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም መድኃኒት፣ ምግብና ሌሎች ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶችን በዝቅተኛ የአየር ሁኔታ እንዳይበላሽ ለማቆየት የሚያስችሉ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን አማካሪ አቶ ዳዊት ፈለቀ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ፍላጎቱን ያሳየው ድርጅት መደበኛ የሚባል ስምምነት ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ሆነ የመሬት ስምምነትን ደግሞ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር እስካሁን ባይፈራረምም፣ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ የቢዝነስ ጥናቱን ሲሠራ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡

ከሌሎች ሴክተሮች በተለየ የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ከማቆያና ማቀዝቀዣ ቦታዎች ጋር ተያይዞ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ውድ እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳዊት፣ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ምላሹ ይህንን ክፍተት ግዙፍ በሆነ መልኩ ማቅረብን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከመድኃኒቶች በተጨማሪ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ ሥጋ ተዋጽኦዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡም ሆነ ከአገር ሊወጡ ሲሉ በተገቢው መንገድ እንዲቀመጡ ከማድረግ በሻገር፣ በአገር ውስጥም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረገውን የማጓጓዝ አገልግሎቶችን ማቅረብን ኢንቨስትመንቱ ታሳቢ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በለማው ቦታ ላይ አርች ኮልድ መሠረተ ልማቱን እንዲያከናውን ሁኔታዎችን ያመቻቸ ሲሆን፣ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱ ከአራት እስከ ስድስት ሔክታር የሚደርስ መሬት ፍላጎት እንዳቀረበ ተገልጿል፡፡

ኢንቨስትመንቱን ለማከናወን ያሰበው ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2022 የመጀመርያው ሩብ ዓመት ውስጥ የለማ መሬት በመረከብ፣ ቀጥሎ ባሉት 18 ወራት ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ የመግባት ዕቅድን ያነገበ እንደሆነ አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ ከ370 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የተቀመጠ ሲሆን፣ አርች ኮልድ  ጥናቶችን ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ ኢንቨስትመንት ሒደቱ ለመግባት ፍላጎቱ ጥሩ የሚባል እንደሆነ ተጠቅሶ፣ በኬንያ ውስጥ በናይሮቢና ሞንባሳ ከተሞች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን የመተግበር እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አማካሪው ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ከማቀዝቀዣ ኢንቨስትመንት ጋር የተገናኘው እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥቂት ቦታዎች ተወስኖ የሚገኝ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ዳዊት፣ የኢንቨስትመንቱ መምጣት እንደታሰበው ከ12 ሺሕ በላይ ፓሌቶችን ተክሎ የሚንቀሳቀስ ይሆናል ተብሎ እንደመጠበቁ ትልቅ የሚባል ኢንቨስትመንት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፍላጎት ያሳየው ድርጅት በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላሉ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከድኅረ ምርት በኋላ የሚበላሹ ምርቶችን ለሚያመርቱ አካላት ጥሩ አማራጭ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ በተለያዩ አገሮች ላይ ፕሮጀክቶችን የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፣ የድርጅቱ ስም አርች ሲባል የአፍሪካ ልማት ባንክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ፋይናንስ የሚደረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡