የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደረቅ ጭነት ላይ ዋጋ ጨመረ | Ethiopian Reporter Tenders | 2merkato | ጨረታ

በነዳጅ ምርት ላይ የሚጣለው ታክስ እየጨመረ በመምጣቱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደረቅ ጭነት የአገልግሎት ዋጋ ላይ የተወሰነ ጭማሪ ማድረጉንና በሌሎች አገልግሎቶቹም ላይ ተመሳሳይ ጭማሪ እንዳደረገ አስታወቀ፡፡ ይህንን አዲሱን ታሪፍም ከሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚተገበር በተለይ ለደረቅ ጭነት አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ በላከው መልዕክት አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ በጭነት አገልግሎቱ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ለአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞቹ ባሳወቀበት መልዕክቱ፣ በእያንዳንዱ የደረቅ ጭነት ዕቃ ላይ በአንድ ኪሎ ግራም ይከፈል የነበረውን 0.40 ዶላር ማድረጉን ያመለክታል፡፡ ጭማሪውን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ደንበኞች እንደለገጹት፣ ጭማሪውን በተመለከተ ከአየር መንገዱ ያገኙት መረጃ፣ አሁን በአንድ ኪሎ 0.40 ዶላር የሆነው፣ ቀደም ብሎ 0.21 ዶላር ሲከፈልበት የነበረውን ነው፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ጭማሪው በአንድ ኪሎ 0.19 ዶላር እንደሆነ ተገልጾላቸዋል፡፡ ይህ ዋጋ የዕቃ መላኪያውን ዋና ዋጋ የሚያካትት ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች አገልግቶቹ በተለየ የጭነት አገልግሎት ታሪፉን ነጥሎ ጭማሪ መጠኑን ያሳወቀ ሲሆን፣ በሌሎች አገልግሎቶችም ላይ ያደረገውን ጭማሪ መጠን እስካሁን አልገለጸም፡፡

ይህ የዋጋ ጭማሪ በቶሎ ሊበላሹ የሚችሉ እንደ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶችን የማይመለከት ቢሆንም፣ ለእነሱም የዋጋ ለውጡ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌሎች ማንኛውም ደረቅ የሚባሉ ምርቶች ግን የሚስተናገዱት በአዲሱ ዋጋ ተመን እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለአየር መንገዱ አሠራር ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደገለጹት እንዲህ ያለው የዋጋ ማሻሻያ የነደጅ ዋጋ ሲጨምር የሚደረግ ማስተካከያ የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ የሚፈጥረው ጫና ከፍ ካለ አየር መንገዱ ወደ ማስተካከያ ዕርምጃ በመግባት ዋጋውን ይጨምራል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነዳጅ ዋጋው ጭማሪው አነስተኛ በመሆኑ አየር መንገዱ ወጪን በራሱ ሲሸፍን ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ጭማሪው ከፍ በማለቱ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ የተለመደና የሚጠበቅ ነው ይላሉ፡፡  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አበባ ያሉ በቶሎ ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶችን ወደ አውሮፓ ለማጓጓዝ በአንድ ኪሎ 1.75 ዶላር በማስከፈል በዚህ ዋጋ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ ቆይቷል፡፡  

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን ይፋ ባደረገበት መረጃው፣ ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎች የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ መስከረም 2014 ዓ.ም. ይሸጥበት በነበረው ዋጋ እንዲቀጥሉ አስታውቆ ነበር፡፡

የአውሮፕላን ነዳጅ ግን በአዲስ አበባ ላይ በመስከረም ወር ሲሸጥበት ከነበረው 45 ብር ከ76 ሳንቲም ወደ 47.43 ሳንቲም ከፍ እንዲል መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የአውሮፕላን የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ተከታታይ ወሮች ዋጋው እየጨመረ የመጣ መሆኑን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፣ ጥቅምት ወር ላይ 47 ብር ከ43 ሳንቲም የነበረው ዋጋ ግን በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. 48 ብር ከ22 ሳንቲም፣ በሐምሌ 2013 ዓ.ም. ደግሞ 51 ብር ከ76 ሳንቲም እንደነበር ይታወሳል፡፡ በመስከረም በ2013 ዓ.ም. የአንድ ሌትር የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ 47 ብር ከ43 ሳንቲም እንደነበር ይታወሳል፡፡