ዳሸን ባንክ ከኢትዮጵያ ውጭ ለንግድ ሥራ የሚጓዙ ደንበኞቹ ግብይታቸውን በውጭ ምንዛሪ ለመፈጸም የሚያስችላቸው የዴቢት ካርድ ይፋ ሲያደርግ፣ አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ዓይነ ሥውራን የሚገለገሉበት ኤቲኤም አገልግሎት ላይ አዋለ፡፡
ሁለቱ ባንኮች ሐሙስ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉዋቸው አዲሶቹ አገልግሎቶቻቸው በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የሚተገበሩ ስለመሆናቸው ባንኮቹ በሰጡዋቸው መግለጫዎች አመልክተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ አሜሪካን ኤክስፕሬስ የተሰኘውን የዴቢት አገልግሎት ካርድ በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ አገልግሎቱን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮች ለውጭ ተጓዦች እንዲህ ዓይነት ካርድ ያዘጋጁ ባለው መሠረት ነው፡፡
ይህ የካርድ አገልግሎት ደንበኞች በየትኛውም ዓለም ግብይት ለመፈጸም ሲሹ በውጭ ምንዛሪ መጠቀም የሚያስችላቸው በመሆኑ እንደ ቀድሞው ጥሬ የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ይዘው መጓዝ እንደማያስፈልጋቸው የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ አዲስ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ አካውንት ያላቸው ደንበኞቻቸው በካርዱ በውጭ አገሮች የሚፈልጉትን አገልግሎት በውጭ ምንዛሪ እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የዴቢት ካርዱ ሁለት ዓይነት ሲሆን፣ አንደኛው ደንበኞች ከውጭ ምንዛሪ አካውንታቸው ጋር የተገናኘ ሆኖ ከዚህ አካውንት ብሔራዊ ባንክ በሚፈቀደው መሠረት አሥር በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው፡፡ ሁለተኛው ካርድ ወደ ውጭ የሚጓዙ ደንበኞች የሚፈቀድላቸውን የውጭ ምንዛሪ በካርዱ ላይ እንዲሞላ ተደርጎ በውጭ ጉዟቸው ካርዱን በመጠቀም አገልግሎት የሚያገኙበት ስለመሆኑም የአቶ አስፋው ማብራሪያ ያመለክታል፡፡
ዓለም አቀፍ የዴቢት አገልግሎት ካርዱ ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያየ የዓለም ለንግድ ሥራ የሚጓዙ ደንበኞች ግብይታቸውን በውጭ ምንዛሪ ለመፈጸም የሚያስችል ነው፡፡
እንደ አቶ አስፋው፣ ዳሸን አሜሪካን ኤክስፕረስ ለዓለም አቀፍና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት ለሚያስተናግዱ ተቋማት በጣም አመቺና አስፈላጊ ካርድ ነው፡፡ ደንበኞች ከኢትዮጵያ ውጭ ሆነው ከውጭ ምንዛሪ አካውንታቸው በቀላሉ ገንዘብ በማውጣት ግብይት መፈጸም ይችላሉ፡፡
ማንኛውም ማንነቱን የሚገልጹ ሕጋዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚችልና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ማዕቀብ ያልተጣለበት ግለሰብም ሆነ ተቋማት ካርዱን መጠቀም እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
በአፍሪካ የአሜሪካን ኤክስፕሬስ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ጄምስ ዋይናይና ይህንን አገልግሎት በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ካርዱ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ አስተማማኝና ቀላል በሆነ መንገድ ዓለም አቀፍ ክፍያ መፈጸም እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ካርዱ በዓለም አቀፍ ዝውውር ወቅት ከፖስ ማሽኖች ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል በመሆኑ ይበልጥ አመቺ እንደሚያደርገውና ዓለም አቀፍ ግብይት ለመፈጸም፣ የሆቴል አገልግሎት ለማግኘትና የአየር በረራ ትኬት ለመቁረጥ አመች መሆኑንም ለአብነት ስለመጥቀሳቸው የዳሸን ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
ባንኩ እንደ አሜሪካን ኤክስፕሬስ፣ ቪዛ፣ ማስተር ካርድና ዩኒየንፔይ ከተሰኙ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር እንዲሁም እንደ ዌስተርን ዩኒየን፣ መኒግራም፣ ኤክስፕሬስ መኒ፣ ዲሃብሺል፣ ኢዝረሚት፣ ትራንስፋስት፣ ወርልድሬሚትና ሪያ ከሚባሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ለዓይነ ሥውራን ደንበኞቹ በድምፅ የታገዘ የኤቲኤም አገልግሎት ጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ለባንክ ኢንዱስትሪው የመጀመርያ የሆነውን ይህንን አገለግሎት ባስጀመረበት ወቅት እንደተገለጸው፣ አቢሲኒያ የአምስት ዓመት ሥልታዊ ዕቅዱን ሲነድፍ ለደንበኞች ምቾቱን የጠበቀና የላቀ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ለዲጂታል ሥርዓት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡
ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ (አቢሲኒያ ኦንላየን)፣ ኢኮሜርስ ፔይመንት፣ ቨርቹዋል ባንኪንግ የተባሉ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞችና ለባንክ ማኅበረሰቡ ያስተዋወቀው ባንኩ፣ የኤቲኤምና የፖስ ማሽኖችን ቁጥር በማሳደግ ረገድም አጥጋቢ ውጤት አስመዝግቤያለሁ ብሏል፡፡
ባንኩ ለዓይነ ሥውራን ያስተዋወቀው የኤቲኤም አገልግሎት ካርዳቸውን በማስገባትና በኤቲኤም ላይ በሚገኘው የድምፅ ማዳመጫ ቦታ ላይ የጆሮ ማዳመጫ በማድረግ የተዘጋጁ መመርያዎችና ምርጫዎችን በመከተል የሚፈልጉትን የባንክ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው ነው፡፡
በዚህ በድምፅ በታገዘ የኤቲኤም የባንክ አገልግሎት ዓይነ ሥውራን ደንበኞች ያለ ምንም ረዳት በራሳቸው የባንክ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ አገልግሎቱ ደንበኞች ገንዘብ ወጪ ማድረግ፣ ገንዘብ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ ማስተላለፍ፣ የሚስጥር ቁጥር መቀየር፣ አጭር የሒሳብ መግለጫ ማተምና ገንዘብ ወደ ቴሌ ብር መላክ የሚያስችላቸው ነው፡፡
አገልግሎቱ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የቀረበ ሲሆን፣ ዓይነ ሥውራን፣ ማንበብ የማይችሉ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያቶች የማየት አቅማቸው የደከመ ሰዎች ከሌሎች የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚዎች እኩል የተሟላ አገልግሎት በመረጡት ቋንቋ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡
ይህን አገልግሎት ለመጠቀም የአቢሲኒያ ባንክ ካርድ፣ የሌሎች ባንኮች ካርዶች እንዲሁም እንደ ማስተር ካርድ፣ ቪዛ ካርድ ቻይና ዩኒየን ፔይ ካርድ ያሉ ዓለም አቀፍ ካርዶች የያዘ ማንኛውም ግለሰብ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻልም ታውቋል፡፡