ዳሸን ባንክ ዳያስፖራው የውጭ ገንዘብ የሚልክበትን ሥርዓት ዘረጋ | Ethiopian Reporter Tenders | 2merkato | ጨረታ

በሕጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ ሬሚታንስ በዓመት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ከዳያስፖራው ወደ አገር ቤት በሕጋዊ መንገድ ከሚላከው ምንዛሪ ይልቅ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚላከው የገንዘብ መጠን ብልጫ አለው ተብሎም ይታመናል፡፡

ወደ አገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ ሕጋዊ መስመርን ተከትሎ በባንክ በኩል ላለመላኩ አንዱ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል ሲላክ የሚጠየቀው የአገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ዌስተርን ዩኒየን፣ መኒ ግራምና መሰል የገንዘብ አስተላላፊዎች በእነሱ በኩል ገንዘብ ሲላክ ለዚያ አገልግሎታቸው ከ10 በመቶ እስከ 15 በመቶ የአገልግሎት ዋጋ ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ ብዙዎች በእነዚህ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ ከመላክ መደበኛ ያልሆነውን መንገድ ተጠቅመው ገንዘብ ወደ አገር ቤት መላክን ይመረጣሉ የሚሉም አሉ፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ግን ለአገርም ጉዳት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለጥቁር ገበያ መስፋፋት ምክንያት እንደሆነም ይታመናል፡፡

ከውጭ ወደ አገር የሚገባው ሬሚታንስ አላላክም ሆነ እዚህ የሚፈለገው ሰው ጋር የሚደርስበት መንገድ የተለየ መግለጫ ቢኖረውም ብዙዎች አሁንም መደበኛውን የባንክ አገልግሎት በመጠቀምና ባለበት ቦታ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር በመሄድ ገንዘብ እየላኩ ስለመሆኑ ማሳያው በሬሚታንስ በዓመት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ይገኛል የሚለው መረጃ ነው፡፡ ከውጭ ወደ አገር የሚመጣን የውጭ ምንዛሪ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዳሸን ባንክ አዲስ አገልግሎት ይዞ መምጣቱን አስታውቋል፡፡

ዳሸን ባንክ ከውጭ ወደ አገር የሚላክን ገንዘብ እስካሁን ሲሠራበት ከነበረው አሠራር በተለየ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን አሠራር የተገበረው በአፍሪካ የክፍያ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን እየመራ ከሚገኘው ፍለተርዌቭ ኩባንያ የዲጂታል ዋሌት መገልገያ አሞሌ ጋር አጋርነት በመፍጠር ነው፡፡ ይህም አሞሌን በመጠቀም በአሞሌ ዋሌት፣ በባንክ ሒሳቦች እንዲሁም ከ2,500 በላይ ባሉ የገንዘብ ማውጫ ቦታዎች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲተላለፍ የሚያስችል ነው፡፡

ከፍለተርዌቭ ጋር የተመሠረተው አጋርነት በዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለሚልኩ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የገንዘብ ማስተላለፍ ሒደቱን በማቅለል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ይደግፋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊዎች፣ ፍለተርዌቭን የሚጠቀሙ የንግድ ተቋማት፣ እንዲሁም የፍለተርዌቭ ባርተር አገልግሎት ተጠቃሚዎች በዚህ አጋርነት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ የሚያስችላቸው መሆኑን የሚጠቁመው፣ የባንኩ መረጃ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የገንዘብ ማስተላለፍ ሒደት ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ ውድ ከመሆኑ በተጨማሪ አሰልቺ የወረቀት ሥራውንና የሚከሰቱ መዘግየቶችን ተከትሎ አስቸጋሪና ብዙ ጊዜ የሚወስድ እንደነበር የባንኩ መግለጫ ያመለክታል፡፡

ይኼ አጋርነት ያለምንም ክፍያ ወዲያውኑ ገንዘብን በፈለጉበት ቦታና ጊዜ መቆጣጠር ወይም ማየት በሚችሉበት መልኩ ማስተላለፍ እንዲችሉ በማድረግ ከውጭ ወደ አገር የሚገባውን ገንዘብ በቀላሉ የሚያቀላጥፍ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የሞኒታ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የምሩ ጫንያለው እንዳሉት፣ አሁን ይፋ በተደረገው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ገንዘብ በሚላክበት ጊዜ ላኪውም ሆነ ተቀባይ ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ አይጠየቁበትም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግጋትን ተከትሎ የሚካሄድ አገልግሎት ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊጠቀምበት የሚያስችል ነው፡፡

የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው ስለ አገልግሎቱ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ዳያስፖራው በዚህ መተግበሪያ ሲጠቀም እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎች ጋር መሄድ ሳያስፈልገው ቀጥታ በሞባይላቸው አፕልኬሽኑን በመጠቀም ወደ አሞሌ ገብተው ገንዘብ ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡  

‹‹በአገር ደረጃ የውጭ ምንዛሪ በጣም የሚፈለግ ነው፤›› ያሉት አቶ አስፋው፣  አሁን ባለው መረጃ በሬሚታንስ በዓመት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ይገባል፡፡ ይህ በተሳለጠ መንገድ እንዲመጣ ሥርዓት ከተዘረጋለት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር እንዲገባ የሚያስችል ነው፡፡ ስለዚህ በትክክለኛው መንገድ ገንዘብ ወደ አገር ቤት እንዲደርስ የሚያደርግ በመሆኑ ለአገር ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ዲጂታልን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ሲቀርብለት ደግሞ የበለጠ እየተጠቀመ በመሄድ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር የሚገባውን ገንዘብ እያደገ እንዲሄድ ማስቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

የፍለተርዌቭ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦለግቤንጋ አግቡላ ደግሞ፣ “ዲጂታል የሆነ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ከዳሸን ባንክና ሞኔታ ቴክኖሎጂስ ጋር በመሥራታቸው በአገሪቱም ሆነ በአኅጉሩ ያለውን የተለያዩ የኢኮኖሚ ደረጃዎች ተሳትፎ ክፍተት ለማጥብበ በሚደረገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ነው፤›› ብለውታል። በጣም የምንተጋለት አንዱ ግባችን በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ ተቋማት ከመላው ዓለም እንዲከፈሉ በማስቻል ንግዳቸውን የሚያሳድግ ትልልቅ የዕድል በሮችን መክፈት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከውጭ ወደ አገር ቤት በቀላሉ ገንዘብ ለማስተላለፍ የተጀመረው ሥራ ገና ጅማሬው መሆኑንም በመግለጽ፣ ‹‹አጋርነታችንን ከዚህ በበለጠ በማጥበቅ በሁሉም ቦታ ያሉ አፍሪካውያንን ለመጥቀም ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በትስስር የጀመሩት ሥራ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ኢኮሜርስን (የኤሌክትሮኒክ ግብይትን) በማስቻል ለዲያስፖራ ማኅበረሰቡ ትልቅ ሚናን ይጫወታል ያሉት አቶ አስፋው፣ ዳሸን ባንክ በዚህ አገልግሎት መምጣቱ ለብቻው ሌሎች ተሿሚዎች ሳይኖሩበት ከውጭ ወደ አገር የሚገባን ገንዘብ ለማስተላለፍ ያስችለዋል፡፡

‹‹ከፍለተርዌቭ ጋር በመሥራት ቴክኖሎጂዎቻችንን ተጠቅመን ለዲያስፖራው ማኅበረሰብ፣ ለደንበኞቻችን እንዲሁም ለነጋዴዎች ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትና ንግድን ዕውን ለማድረግ በጣም ጓጉተናል፤›› ያሉት አቶ የምሩ ደግሞ፣ ዕንከን የለሽና ተጓዳኝ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትን ለመፍጠር ያደረግነው ጥረታችን በኢትዮጵያ በተለያየ የኢኮኖሚ ደረጃ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ይጨምራል፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት መሠረት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባንክ አገልግሎቶችን የማይጠቀም ሲሆን፣ ወደ 40 በመቶ የሚጠጉ የባንክ ቅርንጫፎች በሙሉ የሚገኙት በመዲናዋ አዲስ አበባ ነው። በሦስቱ ተቋማት መካከል የተፈጠረው ትስስር ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች የገንዘብ ማስተላለፍ ሒደቱን በማመቻቸት አነስተኛና እያደጉ ላሉ ንግዶች ዕድሎችን በመስጠት መዳረሻውን ላላገኙ ለእነዚህ የኅብረተሰቡ ክፍል ጠቃሚ አገልግሎትን ይሰጣል። ተጠቃሚዎች ፈቃድ ካላቸው 2,500 የአሞሌ ወኪሎች ገንዘብ መውሰድ ስለሚችሉ በአገሪቷ በተለያየ የኢኮኖሚ ደረጃ ያሉ ሰዎች ተሳትፎ ይጨምራል።

ዳሸን ባንክ ከሌሎች ባንኮች በተለየ የራሱን የገንዘበ ማስተላለፍ ሥራ መጀመሩ በርካታ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች በተለያየ መንገድ የገለጹት ሲሆን፣ በተለይ እስካሁን በነበረው አሠራር እንደ ዌስተርን ዩኒየን ባሉ ኩባንያዎች ገንዘብ ወደ አገር ቤት ሲላክ ባንኮች የሚወዳደሩት በአየር ላይ ስለነበር የዳሸን ባንክ አገልግሎት ይህንን የአየር ላይ ውድድር እንዲቀንስ ያስችላል፡፡

ከአቶ አስፋው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ እስካሁን በነበረው አሠራር ባንኮች ከውጭ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊዎች የሚላከውን ገንዘብ የሚያገኙት በዕድል መሆኑ ነው፡፡ ገንዘቡን የሚያወጣው ሰው ከፈለገው ባንክ ቀርቦ መውሰድ ስለሚችል በዚህ ረገድ ያለው ውድድር የዚህ አገልግሎት መጀመር ጥቁር ገበያን ብቻ ያስቆማል ማለት አይደለም ያሉት አቶ የምሩ፣ ለመኒ ግራም፣ ዌስተርን ዩኒየንና ሌሎች 10 በመቶ ይከፍል የነበረውን ይቀንሳል፡፡ ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ በካርድ የውጭ ምንዛሪ ይዞ መሄድ ነው፡፡